+251944477598 admin@marekospecialweredasito.gov.et

ዜና

የተለጠፉ ዜናዎችን እያዩ

የሊቢዶ ማረቆ ብሔረሰብ የባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየም በቆሼ ከተማ ተጀመረ
October 17, 2026

የሊቢዶ ማረቆ ብሔረሰብ የባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየም በቆሼ ከተማ ተጀመረ

የብሔረሰቡን ቋንቋ፣ ባህላዊ እሴቶችና ቅርሶች ለቀጣይ ትውልድ የማስተላለፍ አስፈላጊነት በሲምፖዚየሙ ትኩረት ተሰጥቶታል።

ቀን፦ ጥቅምት 7 ቀን 2019 ዓ.ም
ቦታ፦ ቆሼ ከተማ፣ ማረቆ ልዩ ወረዳ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል

የሊቢዶ ማረቆ ብሔረሰብ የባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ በማረቆ ልዩ ወረዳ ቆሼ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

ሲምፖዚየሙ የብሔረሰቡን የዘመን መለወጫ የፊተቴ በዓል በማስመልከት እየተካሄደ ሲሆን፣ በዓሉ ነገ ጥቅምት 8 ቀን 2019 ዓ.ም በቆሼ ከተማ በታላቅ ድምቀት እንደሚከበር ተገልጿል።

የሊቢዶ ማረቆ ብሔረሰብ ባህላዊ እሴት የሆነው ፊተቴ፤ ዕርቀ ሰላም የሚወርድበት፣ በደል የሚካስበት፣ ቂምና ቁርሾ የሚወገድበት እንዲሁም ማኅበረሰቡ በአንድነትና በሙሉነት ወደ አዲሱ ዓመት የሚሸጋገርበት ትልቅ ባህላዊ እሴት ነው። በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነትና የሕዝቦች አንድነት መገለጫ ነው።

በቆሼ ከተማ የተጀመረው ሲምፖዚየምና የፓናል ውይይት በሀፋ ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች ምርቃት፣ እንዲሁም በብሔረሰቡ ባህላዊ ክዋኔዎች ታጅቦ ተከፍቷል።

በሲምፖዚየሙ የብሔረሰቡን ባህልና ቋንቋ ከመጥፋት በመጠበቅ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ፣ ባህላዊ እሴቶቹን ለማጠናከርና ማንነቱን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት እየተካሄደ ነው።

በሲምፖዚየሙ ላይ የማረቆ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጀማል አማሮ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደንና አካባቢ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ ደቼ፣ የልዩ ወረዳው ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ሻምበል ደበሮ፣ የልዩ ወረዳው ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳሻው ግዛው፣ የብሔረሰቡ ተወላጅ የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀፋ ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ከአካባቢው ውጭ የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል።

ሲምፖዚየሙ የሊቢዶ ማረቆ ብሔረሰብ ቋንቋን፣ ባህልን፣ ታሪክንና ባህላዊ ጥበብን በማጥናት፣ በመመዝገብና በማስተዋወቅ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ወሳኝ መድረክ ነው።

ፊተቴ፦ ባህላችንን እንጠብቅ፣ ቋንቋችንን እናሳድግ፣ አንድነታችንን እናጠናክር!

ወደ ዜናዎች ተመለስ